Logo
Hamza s1

የመክሊት ታሪክ – ሐምዛ

ዜና
23 ጁላይ 2024
በፍቅር መታለል መጨረሻው ምን ይመስላል?
hamza meklit article

የመክሊት ታሪክ የሚጀምረው በአሳዛኝ መንገድ ተታላ እውነቱን ስትደርስበት ነው። ለጌቶች ቤተሰብ የምትሠራ የአገልጋይ ሴት ልጅ እንደመሆኗ ከአሰሪዎቿ ልጅ መኳንንት ጋር ያላት ግንኙነት እንደ እህት እና ወንድም ነው፣ ነገር ግን መኳንንት ልቧን በመቀየር የሚፈልገውን ይወስዳል።

የመኳንንት እራስ ወዳድነት መክሊትን ወደ የማይሆን አይነት ህይወት ውስጥ ከቷታል። መክሊትን እንደሚወዳት በማሳመን ክብረ ንጽህናዋን ወስዶ ወዲያው ትቷታል። መክሊት በመኳንንት ባህሪ ግራ ብትጋባም እንደሚያገባት እርግጥኛ ነበረች። ነገር ግን የመኳንንት ቤተሰብ መኳንንትን ከአብሮአደጓ አለሜ ጋር ለመዳር እየተዘጋጁ መሆኑን ስትረዳ እልህ ይይዛታል።

መክሊት በተደጋጋሚ መኳንንት እሷ በህይወት እያለች ማንንም ማግባት እንደማይችል ትነግረዋለች። መክሊት በመኳንንት መታለሏ እና በፍቅር እሱን ብቻ ማወቋ ከመኳንንት ጋር ከመሆን ውጪ ምርጫ የላትም ብላ ታምናለች። ስለዚህም አለሜ እና እጮኛዋ ዳኜ በመኳንንት ቤተሰብ ሰርጋቸው እንዲያቆሙ ሲደረጉ እሷ እንዲያመልጡ ትረዳቸዋለች። ግን እነሱን ለመርዳት የምታደርገውን ጥረት መኳንንት ሲሰማ ወንዝ ውስጥ ጥሏት ሞት አፋፍ ላይ ትደርሳለች።

ከወንዝ ውስጥ አውጥቶ ያዳናት አብሮ አደጓ ክንዴ ጋር ይበልጥ ይቀራረባሉ። በዚህ ጊዜ ላይ ክንዴ ከመክሊት ፍቅር ይዞት እንድታገባው ይጠይቃታል። መክሊት ክንዴን ለማግባት አትስማማም ነገር ግን ይህ ስላልወደደችው ሳይሆን ሌላ የደበቀችው ምስጢር ስላለ ነው። ከመኳንንት ያረገዘች መሆኗን እያወቀች ክንዴን ማግባት እንደማትችል ታውቃለች እናም ምርጫ ከማጣቷ የተነሳ መኳንንት የጀመረውን አዲስ የፍቅር ግንኙነት ለማበላሸት ትሞክራለች።

ይህ ስራዋ ግን ልጇን እንድታጣ ሊያደርጋት ነበር ስለዚህም እጅ ሰጥታ ወደ አክስቷ ቤት ተሰዳለች። መክሊት እጅ ሰጥታ ልጇን ለማሳደግ ብትፈልግም ቤተሰቧ እሷ እንደዛ ተጎድታ መኳንንት በደስታ መኖር መቻል የለበትም ብሎ ያምናል። ስለዚህም እውነቱን ለአጥናፍ ያጋልጣሉ ግን እንደጠበቁት ተቀባይነት ሳይሆን ያገኙት፣ መኳንንት ሰርጉ እንዳይበላሽ መክሊትን ለማስወገድ ይነሳል።

መክሊት በድጋሜ በመኳንንት ትታለል ይሆን? ወይስ ልጇን እና እራሷን መከላከል ትችላለች?

የመጨረሻውን የሐምዛ ክፍል ማክሰኞ ከምሽቱ 3፡00 በአቦል ቲቪ ፣ ዲኤስቲቪ ቻናል 465 ይቀርባል! የመክሊት መጨረሻ እንዳያመልጥዎ።